ኑሮዬ ከተወለድሁበት እትብቴ ከተቀበረበት መንደር ሰፈር ቀዬ በጣም ሩቅ ነው። ያባት ያያቴ አህያ ረግጦት በማያውቅ የሰው ሀገር። ምናልባት እንደ ቡድሃወች እና እንደ ሂንዱዎች እምነትና እሳቤ ነፍሳት ደግመው ደጋግመው አፈር ለብሰው እና ልሰው ቢወለዱ እንኳን ያባት ያያት የቅመአያቶቸ አህዮች አሁን በምኖርበት ሀገር አንድም ግዜ ስንኳ ተወልደው አገሩን ሰርዶ ግጠውበታል ብዬ አላምንም፤ አላስብምም፤ … ያለዚያማ እነሱ ጠልተውት ባባቶቼ ባድማ ከተወለዱ፣ በፍጥረት ላዕላይ ያለሁት ፍጡር እኔ እንደምንስ ብዬ ላየው እና ልኖርበት አስብና እመኝ ነበር?!…..
እንግዲህ ኑሮዬ በባዕድ ሀገር ቢሆንም ላንድ የተቀደሰ/የተደጎሰ ምግባር ባለቃችን ፈቃድ ለትውልድ አገሬ ሰፈር መንደሬ ወደሚቀርብ አገር ሄድን። መዳረሻችን ግን በፊትም አሁንም ወደፊትም ሳስበው “ረ” ቅርጽ ያለው መንገድን የተከተለ ነው። ከዚያም እትብቴን ብሻው ብዬ ሳስብ የትውልድ ቀዬዬ ልክ “ሩ”ን የመሰለ መንገድን መከተል ነው። ከዛም ከች ነው….
መሄድን ተመኘሁ። መንጎድ አማረኝ። እሽክም ማለት።…… ነጎድሁ፣ ወደትውልድ ቀዬዬ።……….
በአካልም በመንፈስም መራቄን፣ መለዬቴን የተረዳሁት ግን አንዱንም ሁነት ሳላውቅ ይህን ያህል ዘመን በመኖሬ ነው።
እናትና አባቴ ተለያይተዋል። ለኔ መርዶ ይሁን ምን፤ እውን ይሁን ህልም አላውቅም። ግን መሆኑን ከእህት ወንድሞቼ ተነገረኝ። አባቴ ወደከተማ ጠጋ ብሎ ብዙዎችን እህትና ወንድሞቼን ሰብስቦ ይኖራል። አላገባም። ከብቶች ያረባል። ጥሩ የወተት ምርት እና ትንሽም የንባብ መጻህፍትን እየነገደ የተሻለ የተባለ ኑሮ ይኖራል። ስለኑሮው ስጠይቃቸው እህቶቼ እና ወንድሞቼ የመለሱልኝ ነው። ታላቋ እህቴ ግን አሁንም እርጥቡን ከደረቅ ማግዳ እንጀራ ልትጋግር ደፋ ቀና ትላለች። እሳቱ አልነድ ብሎ አስሸግሯታል።…. ኑሮ…..። በዚህም ውስጥ ያች የተረገመች ነፍስ ከስጋ ውሻቅ ውስጥ እድሜዋን ታራዝም ዘንድ ትፍገመገማለች። ያለዚያማ ምግብ ለምን ያስፈልግ ነበር? እርጥብ ከደረቅ ማግዶ በእንጀራ ስም እንደጃርት በጢስ መታፈን፣ የነፍስን የኃጥያት እና መርገምት የፍዳ ቅጣትን ዘመን ከመጨረስ በማይለዬ የኑሮ ማጥ ውስጥ የተለዬ ፋይዳ የተለዬስ ትርጉም ሊኖረው ይሆን?
እናቴ ግን ራቅ ወዳለ ቦታ ሄዳ ሌላ ባል እንዳገባች ሰማሁ። የቤተሰቡን የመጨረሻ ልጅ ይዛ። ማወቅ ፈለግሁ። በጣም። ነገሮች ሁሉ ተደናገሩኝ።…. ሁሉን ማወቅ ፈለግሁኝ። ሁሉንም። ጥያቄዎች ያለወረፋ ተጋፍተው መጡ። ካንደበቴ ግን አንዱም መውጣት አልቻለም…. በጣም ይጋፋሉ እና ነው። በዚህ መሃል ከእንቅልፌ ስነቃ፣ ሰውነቴ ድቅቅ ብሏል። አንድም መገጣጠሚያ በጅማት የተቋጠረ አይመስልም፣ ስነሳ የተሰማኝ ስሜት። ይህ ሁነት ህልም ቢሆንም ይህን ያሳዬኝን እንቅልፍ አይጠሉ ጠላሁት። በቃ ጠላሁት። አቅለሸለሸኝ። ይህን ያሳዬኝንም ጸለምተኛ አስተሳሰብ የተሸከመ ጭንቅላቴን ቆርጦ መጣል አሰኘኘ። ራሴን ጠላሁት። ረገምሁት።
ፍጹም ጸለምተኛ አስተሳሰብ….
የላስታ ላሊበላ፣ የዋግ የሰቆጣ ፣ የራያ …. ወሎ፣ … ጎንደር ጎጃም እያልሁ በባህል ዘፈን መርገፍ ያዝሁ… መርገፍገፍ። ይህ የመርግ ያህል የተሰማኝ ትኩስ የህልም ስሜት ቅልል እስኪልልኝ። እንግዲያው ጸሎትስ አልሻም። ይህን ያሳዬኝ ሴጣን ነው አልልም እና። እናም ቅልል አለኝ። ይህን የባህል ጭፈራ ስለጨፈርሁም እናቴን ያከበርኋት፤ የካስኋትም ያህል ተሰማኝ። ግን ቢራ አምሮኛል፤ እንዳማረኝም እስካሁን አልጠጣሁም። ለክፏዋ ስሜት ብክንክን እንግብግብ ለምታደርገዋ የመበደል እና የበዳይ ስሜት ማስረሻ ማስታገሻዋ ያችው ውብ የወይንጠጅ ናትና ነው…..
(March 15, 2013)